1 ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በባቢሎን ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ሰጠ።
2 በሜዶን አውራጃ በሚገኘው በአሕምታ ከተማ አንድ ጥቅልል ብራና ተገኘ፤ በውስጡም እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎበት ነበር፤ማስታወሻ፤
3 በንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የእግዚእብሔር ቤተ መቅደስ ንጉሡ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ ሆኖ እንደ ገና ይሠራ፤ መሠረቱም ይጣል፤ ቁመቱ ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱም ሥልሳ ክንድ ይሁን፤
4 በሦስት ዙር ታላላቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር ዕንጨት ይሠራ፤ ወጪውም ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል።
5 እንዲሁም ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች፣ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቦታቸው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለሱ ይሁን፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይቀመጡ።
6 አሁንም በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የሆንኸው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና እናንተም በዚያ አውራጃ የምትገኙ ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ወደዚያ አትድረሱ።
7 በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት።