ዕዝራ 6:12-18 NASV

12 ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው።እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

13 ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ።

14 ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ።

15 ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

16 ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ።

17 ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ።

18 በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር አገልግሎት ካህናቱን በየማዕረጋቸው፣ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቧቸው።