15 ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።
16 ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ።
17 ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ።
18 በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር አገልግሎት ካህናቱን በየማዕረጋቸው፣ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቧቸው።
19 ምርኮኞቹ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ።
20 ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ሁሉም በሥርዐቱ መሠረት ነጽተው ነበር። ሌዋውያኑም የፋሲካውን በግ ለምርኮኞቹ ሁሉ፣ ለካህናት ወንድሞቻቸውና ለራሳቸው ዐረዱ።
21 ስለዚህ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በአምልኮ ይፈልጉት ዘንድ ራሳቸውን ከአረማውያን ጎረቤቶቻቸው ርኵሰት ከለዩት ሁሉ ጋር በሉ።