ዕዝራ 6:4-10 NASV

4 በሦስት ዙር ታላላቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር ዕንጨት ይሠራ፤ ወጪውም ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል።

5 እንዲሁም ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች፣ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቦታቸው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለሱ ይሁን፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይቀመጡ።

6 አሁንም በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የሆንኸው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና እናንተም በዚያ አውራጃ የምትገኙ ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ወደዚያ አትድረሱ።

7 በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት።

8 በተጨማሪም የአይሁድ መሪዎች ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና ሲሠሩ፣ እናንተ ምን እንደምታደርጉላቸው ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ሥራውም እንዳይቋረጥ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከኤፍራጥስ ማዶ ከሚገኘው ገቢ ላይ ይከፈል።

9 ለሰማይ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ማለት ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ተባዕት ጠቦቶችን ስጧቸው፤ እንዲሁም ስንዴው፣ ጨዉ፣ የወይን ጠጁና ዘይቱ በኢየሩሳሌም ያሉት ካህናት በሚጠይቋችሁ መሠረት ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ይሰጣቸው።

10 ይህ የሚሆነው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ ለንጉሡና ለወንድ ልጆቹም ደኅንነት እንዲጸልዩ ነው።