ዕዝራ 8:25-31 NASV

25 ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው።

26 ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣

27 አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው።

28 እንዲህም አልኋቸው፤ “እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው።

29 ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።”

30 ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ።

31 እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን።