29 ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።”
30 ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ።
31 እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን።
32 ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ዐረፍን።
33 በአራተኛው ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱን በአምላካችን ቤት መዝነን ለኦሪዮ ልጅ ለካህኑ ለሜሪሞት በእጁ አስረከብነው፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፣ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ።
34 ሁሉም ነገር ተቈጠረ፤ ተመዘነም፤ የተመዘነውም ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ተመዘገበ።
35 ከዚያም ከምርኮ የተመለሱት፣ ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፣ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፣ ሰባ ሰባት ተባዕት ጠቦቶችን፣ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር።