ዮናስ 2 NASV

የዮናስ ጸሎት

1 ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

2 እንዲህም አለ፤“ተጨንቄ ሳለሁ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤እርሱም መለሰልኝ፤ከመቃብሩም ጥልቅ ርዳታን ፈልጌ ተጣራሁ፤አንተም ጩኸቴን ሰማህ።

3 ጥልቅ ወደ ሆነው፣ወደ ባሕሩ መካከል ጣልኸኝ፤ፈሳሾችም ዙሪያዬን ከበቡኝ፤ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣በላዬ አለፉ።

4 እኔም፣ ‘ከፊትህ ጠፋሁ፣ነገር ግን እንደ ገና፣ወደ ቅዱስ መቅደስህ፣እመለከታለሁ’ አልሁ።

5 ውሃ እስከ ዐንገቴ አጠለቀኝ፤ጥልቁም ከበበኝ፤የባሕርም ዐረም በራሴ ላይ ተጠመጠመ።

6 ወደ ተራሮች መሠረት ሰመጥሁ፤የምድርም በር ለዘላለም ተዘጋብኝ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤አንተ ግን ሕይወቴን ከጒድጓድ አወጣህ።

7 “ነፍሴ በዛለች ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን ዐሰብሁ፤ጸሎቴም ወደ አንተ፣ወደ ቅዱስ መቅደስህ ዐረገች።

8 “ከንቱ በሆኑ ጣዖቶች ላይ የሚንጠለጠሉ፤ሊያገኙ የሚገባቸውን ጸጋ ያጣሉ።

9 እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።”

10 እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፤ ዮናስንም በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።

ምዕራፎች

1 2 3 4