ዮናስ 3 NASV

ዮናስ ወደ ነነዌ ሄደ

1 የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤

2 “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።”

3 ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ። በዚህ ጊዜ ነነዌ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ እርሷንም ከዳር እስከ ዳር ለመጐብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር።

4 ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ።

5 የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።

6 ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሱንም አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ።

7 ከዚያም እንዲህ ሲል በነነዌ ዐዋጅ አስነገረ፤“ከንጉሡና ከመሳፍንቱ የወጣ ዐዋጅ፤ማንም ሰው ወይም እንስሳ፣ የከብት መንጋም ሆነ የበግ መንጋ፣ ምንም ነገር አይቅመስ፤ አይብላ፤ ውሃም አይጠጣ።

8 ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ።

9 እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ራርቶ ከጽኑ ቍጣው ይመለስም እንደሆነ ማን ያውቃል?”

10 እግዚአብሔርም ምን እንዳደረጉና ከክፉ መንገዳቸውም እንዴት እንደ ተመለሱ ባየ ጊዜ ራራላቸው፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም።

ምዕራፎች

1 2 3 4