ዳንኤል 11:31-37 NASV

31 “የጦር ሰራዊቶቹም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ በዚያም ጥፋትን የሚያመጣውን የጥፋት ርኵሰት ይተክላሉ፤

32 ኪዳኑን የሚተላለፉትን በማታለል ያስታል፤ አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ እርምጃም ይወስዳሉ።

33 “ለጊዜው በሰይፍ ቢወድቁም፣ ቢቃጠሉም፣ ቢማረኩና ቢዘረፉም፣ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ብዙዎችን ያስተምራሉ።

34 በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ ርዳታ ያገኛሉ፤ እውነተኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችም ይተባበሯቸዋል።

35 ጥበበኛ ከሆኑ ሰዎች አንዳንዶቹ ይሰናከላሉ፤ ይህም እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የጠሩ፣ የነጠሩና እንከን የሌለባቸው ይሆኑ ዘንድ ነው፤ የተወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰምና።

36 “ንጉሡ ደስ እንዳለው ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ራሱን እጅግ ከፍ በማድረግ በአማልክት አምላክ ላይ ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የቊጣውም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ የተወሰነው ነገር ሁሉ መሆን አለበትና።

37 ሴቶች ለሚወዱትም ሆነ ለአባቶቹ አማልክት ክብርን አይሰጥም፤ ማንኛውንም አምላክ አያከብርም፤ ነገር ግን ራሱን ከእነዚህ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል።