28 ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤
29 ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ፣ ንጉሡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ ሳለ፣
30 “በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ።
31 ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ፣ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለ አንተ የታወጀው ይህ ነው፤ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዶአል፤
32 ከሕዝብ መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊት ጋርም ትኖራለህ፤ እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመት ያልፋል።”
33 ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጒሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
34 ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት።ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።