ዳንኤል 4:33-37 NASV

33 ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጒሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

34 ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት።ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

35 የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤በሰማይ ኀይላት፣በምድርም ሕዝቦች ላይ፣የወደደውን ያደርጋል፤እጁን መከልከል የሚችል የለም፤‘ምን ታደርጋለህ?’ ብሎ የሚጠይቀውም የለም።

36 አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ፣ ወዲያው ለመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሱልኝ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቴ ፈለጉኝ፤ ወደ ዙፋኔም ተመለስሁ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንሁ።

37 የሰማይ አምላክ የሚያደርገው ሁሉ ትክክል፣ መንገዶቹም ሁሉ ጽድቅ ስለሆኑ፣ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል።