ዳንኤል 6:19-25 NASV

19 በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ እየተጣደፈ ሄደ።

20 ወደ ጒድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ።

21 ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤

22 ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለ ተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ፣ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጐዱኝም።”

23 ንጉሡ እጅግ ተደስቶ፤ ዳንኤልን ከጒድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጒድጓድ በወጣ ጊዜ፣ አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።

24 በንጉሡ ትእዛዝ፣ ዳንኤልን በሐሰት የከሰሱትን ሰዎች፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር አምጥተው፣ በአንበሶቹ ጒድጓድ ውስጥ ጣሏቸው፤ ገና ወደ ጒድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱም፣ አንበሶቹ ቦጫጨቋቸው፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።

25 ከዚያ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈ፤“ሰላም ይብዛላችሁ!