ዳንኤል 7:14-20 NASV

14 ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።

15 “እኔ ዳንኤል በመንፈሴ ታወክሁ፤ ያየሁትም ራእይ እጅግ አስጨነቀኝ።

16 በዚያ ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ፣ የዚህ ሁሉ እውነተኛ ትርጒም ምን እንደሆነ ጠየቅሁት።“እርሱም መለሰልኝ፤ የእነዚህንም ነገሮች ትርጒም እንዲህ ሲል ነገረኝ፤

17 ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤

18 ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።

19 “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጒም ማወቅ ፈለግሁ።

20 ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለ ዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ።