ዳንኤል 7:7-13 NASV

7 “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከእርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት።

8 “ስለ ቀንዶቹ ሳስብ ሳለሁ፣ ከመካከላቸው አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ብቅ ሲል አየሁ፤ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች ሦስቱ ከፊቱ ተነቃቀሉ፤ ይህም ቀንድ የሰው ዐይኖችን የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበረው።

9 “እኔም ስመለከት፣“ዙፋኖች ተዘረጉ፤ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤የራሱም ጠጒር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድ እሳት ነበሩ።

10 የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆይፈስ ነበር፤ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤መጻሕፍትም ተከፈቱ።

11 “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም።

12 ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።

13 “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።