ዳንኤል 7:9-15 NASV

9 “እኔም ስመለከት፣“ዙፋኖች ተዘረጉ፤ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤የራሱም ጠጒር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ፤ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣መንኰራኵሮቹም ሁሉ እንደሚነድ እሳት ነበሩ።

10 የእሳት ወንዝ፣ ከፊት ለፊቱ ፈልቆይፈስ ነበር፤ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል፤የፍርድ ጉባኤ ተሰየመ፤መጻሕፍትም ተከፈቱ።

11 “ቀንዱም ከሚናገረው የትዕቢት ቃል የተነሣ፣ መመልከቴን ቀጠልሁ፤ አውሬው እስኪታረድና አካሉ ደቆ ወደሚንበለበለው እሳት እስኪጣል ድረስ ማየቴን አላቋረጥሁም።

12 ሌሎቹም አራዊት ሥልጣናቸው ተገፎ ነበር፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜና ወቅት በሕይወት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው።

13 “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።

14 ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።

15 “እኔ ዳንኤል በመንፈሴ ታወክሁ፤ ያየሁትም ራእይ እጅግ አስጨነቀኝ።