ዳንኤል 9:2-8 NASV

2 በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ለኤርምያስ በተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የኢየሩሳሌም መፈራረስ ሰባ ዓመት እንደሚቈይ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ።

3 ስለዚህ ማቅ ለብሼ፣ በራሴም ላይ ዐመድ ነስንሼ፣ በጾምና በጸሎት፣ በምልጃም ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ።

4 ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ተናዘዝሁም፤“ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤

5 እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል።

6 ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።

7 “ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን እኛን በበተንህባቸው አገሮች ሁሉ የምንገኝ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምና የመላው እስራኤል ሕዝብ፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለን በዚህ ቀን በኀፍረት ተከናንበናል።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል።