3 አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ፤ ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን?
4 ምክንያቱም አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ቢል፣ ሰብአዊ ፍጡር ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?
5 ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው።
6 እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው።
7 ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም።
8 የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል።
9 እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።