1 ቆሮንቶስ 8:4-10 NASV

4 እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።

5 መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፤

6 ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።

7 ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል።

8 ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።

9 ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ።

10 አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን?