12 ሌሎች ይህን መብት ከእናንተ ማግኘት ከቻሉ፣ እኛ ይበልጥ ማግኘት አይገባንምን?እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይልቁንም ለክርስቶስ ወንጌል ዕንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሣለን።
13 በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን?
14 እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዞአል።
15 እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና።
16 ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ።
17 በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል።
18 ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው።