1 ተሰሎንቄ 1:1-7 NASV

1 ከጳውሎስ፣ ከሲላስና ከጢሞቴዎስ፤የእግዚአብሔር አብና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

2 በጸሎታችን እያስታወስናችሁ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ስለ ሁላችሁ እናመሰግናለን።

3 ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።

4 በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እርሱ እንደ መረጣችሁ እናውቃለን፤

5 ምክንያቱም ወንጌላችን ወደ እናንተ የመጣው በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙም መረዳት እንጂ በቃል ብቻ አይደለም። ደግሞ ስለ እናንተ ስንል በመካከላችሁ እንዴት እንደኖርን ታውቃላችሁ።

6 እናንተ እኛንና ጌታን መስላችኋል፤ ምንም እንኳ ብርቱ መከራ ቢደርስባችሁም ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ተቀብላችኋል።

7 ከዚህም የተነሣ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙ ምእመናን መልካም ምሳሌ ሆናችኋል።