1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውን፣ የሰማነውን፣ በዐይኖቻችን ያየነውን፣ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን።
2 ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም። በአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤
3 እናንተም ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ኅብረታችንም ከአብ፣ ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።
4 ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን።
5 ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው።
6 በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም።
7 ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
8 ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
9 ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።
10 ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።