1 ዮሐንስ 2:18-24 NASV

18 ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።

19 ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።

20 እናንተ ግን ከእርሱ ከቅዱሱ፣ ቅባት አላችሁና፤ ሁላችሁም እውነትን ታውቃላችሁ።

21 እኔ የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፤ ነገር ግን እውነትን ስለምታውቁትና ከእውነት ምንም ውሸት ስለማይወጣ ነው።

22 ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው።

24 ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር፤ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።