1 ጴጥሮስ 2:3-9 NASV

3 ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

4 በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣

5 እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ።

6 ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣በጽዮን አኖራለሁ፤በእርሱም የሚያምን፣ ከቶ አያፍርም።”

7 እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8 ደግሞም፣ “ሰዎችን የሚያሰናክል፣የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ።