3 የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።
4 እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
5 የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ የመብዛቱን ያህል መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል።
6 መከራ ብንቀበል ስለ እናንተ መጽናናትና መዳን ነው። ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል በትዕግሥት እንድትጸኑ ስለ እናንተ መጽናናት ነው።
7 ስለ እናንተ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው፤ ምክንያቱም በመከራችን እንደ ተካፈላችሁ ሁሉ በመጽናናታችንም እንደምትካፈሉ እናውቃለን።
8 ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር።
9 በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።