2 እናንተኮ ሰው ሁሉ የሚያውቃችሁና የሚያነባችሁ በልባችን ላይ የተጻፋችሁ ደብዳቤዎቻችን ናችሁ፤
3 እናንተ በቀለም ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ፣ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይሆን በሰው ልብ ጽላት ላይ የተጻፋችሁና በእኛ የተገለገላችሁ የክርስቶስ ግልጽ ደብዳቤ ናችሁ።
4 በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ይህን የመሰለ ነው፤
5 ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም።
6 እርሱም በፊደል ላይ ሳይሆን በመንፈስ ላይ የተመሠረተውን የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን፤ ምክንያቱም ፊደል ይገድላል፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።
7 እንግዲህ እስራኤላውያን ከፊቱ ክብር የተነሣ የሙሴን ፊት ትኵር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ፣ ያ ከጊዜ በኋላ የሚያልፈውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው የሞት አገልግሎት በክብር ከመጣ፣
8 ታዲያ፣ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ከዚያ የላቀ ክብር አይኖረውም?