2 ተሰሎንቄ 1:1-7 NASV

1 ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ፤በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤

2 ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

3 ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን።

4 ስለዚህ በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥ ታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን።

5 ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።

6 እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤

7 መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው።