1 ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ፤በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤
2 ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን።
4 ስለዚህ በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥ ታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን።
5 ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።
6 እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤
7 መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው።
8 በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።
9 እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ፤
10 የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ዘንድ ሊገረም በሚመጣበት በዚያን ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና።
11 ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ መልካም ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን።
12 ደግሞም እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በእርሱ እንድ ትከብሩ ይህን እንጸልያለን።