2 ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን።
4 ስለዚህ በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥ ታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን።
5 ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።
6 እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤
7 መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው።
8 በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።