1 ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ።
2 ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣
3 ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣
4 ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና።
5 ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ።
6 እነርሱም በየቤቱ ሾልከው እየገቡ የኀጢአት ብዛት የተጫናቸውን፣ በተለያየ ክፉ ምኞት ውስጥ ገብተው የሚዋልሉ መንፈሰ ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ናቸው፤
7 እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ሁል ጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ አይችሉም።