2 ጢሞቴዎስ
ምዕራፎች 4
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤
2ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።
3ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።
4እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።
5አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።
6እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።
7መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።
8ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።