2 ጢሞቴዎስ
ምዕራፎች 2
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1እንግዲህ ልጄ ሆይ፤ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ።
2በብዙ ምስክር ፊት ከእኔ የሰማኸውን፣ ሌሎችን ለማስተማር ብቃት ላላቸው ለታመኑ ሰዎች ዐደራ ስጥ።
3እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር፣ ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል።
4በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላ ልፍም።
5እንደዚሁም በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም።
6ትጉህ ገበሬም ከሰብሉ ለመጠቀም የመጀመሪያው ሊሆን ይገባዋል።
7እኔ የምለውን ልብ በል፤ ጌታ በሁሉም ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና።
8ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው፤
9ለዚህም እንደ ወንጀለኛ እስከ መታሰር ድረስ መከራን እየተቀበልሁ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።
10ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እነርሱም ያገኙ ዘንድ፣ ለተመረጡት ስል ሁሉንም በመታገሥ እጸናለሁ።
11እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፤ከእርሱ ጋር ከሞትን፣ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።
12ብንጸና፣ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን።ብንክደው፣እርሱ ደግሞ ይክደናል፤
13ታማኞች ሆነን ባንገኝእርሱ ታማኝ እንደሆነ ይኖራል፤ራሱን መካድ አይችልምና።