3 ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው።
4 ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀምጦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የሰማችሁትን፣ አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤
5 ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”
6 እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፣ “ጌታ ሆይ፤ የእስራኤልን መንግሥት መልሰህ የምታቋቁምበት ጊዜው አሁን ነውን? ብለው ጠየቁት።
7 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቁ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤
8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”
9 ይህን ካለ በኋላ እያዩት ወደ ላይ ዐረገ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰወረችው።