4 ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ነገሩን በቅደም ተከተል ያስረዳቸው ጀመር፤
5 “በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ በተመስጦ ውስጥ እያለሁ ራእይ አየሁ፤ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር፣ በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ እኔ ወደ ነበርሁበት ቦታ ሲወርድ አየሁ።
6 አተኵሬም ይህን ነገር ስመለከት አራት እግር ያላቸው እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፍ አየሁ።
7 በዚህ ጊዜ፣ ‘ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣና ዐርደህ ብላ’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
8 “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነገር ፈጽሞ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ።
9 “ያም ድምፅ ዳግመኛ፣ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው’ ሲል ከሰማይ ተናገረኝ።
10 ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ከዚያ ሁሉም እንደ ገና ወደ ሰማይ ተወሰደ።