1 ጳውሎስ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ደረሰ። በዚያም እናቱ አይሁዳዊት ሆና በጌታ ያመነች፣ አባቱ ግን የግሪክ ሰው የሆነ፣ ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ።
2 እርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው።
3 ጳውሎስም ይህ ሰው ከእርሱ ጋር እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ አባት የግሪክ ሰው እንደሆነ ያውቁ ነበርና።
4 እነርሱም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን ውሳኔ ተቀብለው እንዲጠብቁ ለምእመናኑ ይሰጡ ነበር።
5 አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር።