8 ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር።
9 አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቶአቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር።
10 ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።
11 እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤
12 መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኵሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።
13 እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኵሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤
14 የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር።