19 ምንም እንኳ ከአይሁድ ሤራ የተነሣ መከራ ቢያደርሱብኝም፣ ጌታን በታላቅ ትሕትናና በእንባ ከማገልገል አልተቈጠብሁም፤
20 በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም።
21 በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም አጥብቄ መስክሬላቸዋለሁ።
22 “አሁንም እዚያ ስደርስ የሚደርስብኝን ባላውቅም፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው።
23 ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል።
24 ይሁን እንጂ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።
25 “አሁንም ቢሆን፣ በመካከላችሁ ተዘዋውሬ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ፣ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲያ ፊቴን እንደማታዩ ዐውቃለሁ።