ሐዋርያት ሥራ 21:29-35 NASV

29 ይህንም ያሉት ቀደም ሲል፣ የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማው ውስጥ ስላዩት፣ ጳውሎስ እርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ ይዞ የገባ ስለ መሰላቸው ነበር።

30 ከተማው በሙሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ከየአቅጣጫው እየተሯሯጡ መጡ፤ ጳውሎስንም ይዘው እየጐተቱት ከቤተ መቅደሱ ግቢ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያውኑ ተዘጉ።

31 ሊገድሉት ሲፈልጉም የኢየሩሳሌም ከተማ ፍጹም ታወከች፤ ወሬውም ለሮማ ጦር አዛዥ ደረሰው።

32 እርሱም ወዲያው አንዳንድ የጦር መኰንኖችንና ወታደሮችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም መኰንኖቹንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ።

33 የጦር አዛዡም ቀርቦ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ጠየቀ።

34 ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ።

35 ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው።