ሐዋርያት ሥራ 23:1-7 NASV

1 ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ።

2 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ።

3 ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላ ስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።

4 ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።

5 ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፎአልና” አላቸው።

6 ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ።

7 ይህንንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ።