ሐዋርያት ሥራ 23:3-9 NASV

3 ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላ ስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።

4 ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።

5 ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፎአልና” አላቸው።

6 ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ።

7 ይህንንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ።

8 ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።

9 ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሕግ መምህራንም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮትስ እንደሆነ ምን ይታወቃል?” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ።