2 የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን።
3 ጳውሎስም ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጨምር፣ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች።
4 የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ።
5 ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጒዳት አልደረሰበትም።
6 ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ።
7 በዚያም ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ አለቃ የፑፕልዮስ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን።
8 የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው።