27 ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤
28 “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።”
29 ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!
30 እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤
31 እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
32 እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።”
33 ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ።