1 ሳውልም በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር።በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ተነሣ፤ ከሐዋርያትም በስተቀር አማኞች በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ አውራጃዎች ሁሉ ተበተኑ፤
2 በመንፈሳዊ ነገር የተጉ ሰዎችም እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ ደግሞም እጅግ አለቀሱለት።
3 ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ታጥቆ ተነሣ፤ ከቤት ወደ ቤት በመግባትም ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ እያወጣ ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።
4 የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ፤
5 ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው።
6 ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር።