30 ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት።
31 በዚህ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም እግዚአብሔርን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቍጥር እየበዛች ሄደች።
32 ጴጥሮስም ከአገር ወደ አገር በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ በልዳ የሚኖሩትን ቅዱሳን ለመጐብኘት ወረደ።
33 በዚያም ኤንያ የተባለ፣ ስምንት ዓመት የዐልጋ ቍራኛ የነበረ አንድ ሽባ ሰው አገኘ።
34 ጴጥሮስም፣ “ኤንያ ሆይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣና መኝታህን አንጥፍ” አለው። ኤንያም ወዲያውኑ ብድግ አለ።
35 በልዳና በሰሮና የሚኖሩትም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ።
36 በኢዮጴ ጣቢታ የተባለች አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጓሜ ዶርቃ ማለት ነው። እርሷም ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር።