ሐዋርያት ሥራ 9:36-42 NASV

36 በኢዮጴ ጣቢታ የተባለች አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጓሜ ዶርቃ ማለት ነው። እርሷም ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር።

37 በዚያ ጊዜም ታማ ሞተች፤ ሰዎችም አስከሬኗን አጥበው በሰገነት ላይ ባለው ክፍል አስቀመጡት።

38 ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለ ነበረች፣ ደቀ መዛሙርትም ጴጥሮስ በልዳ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለት ሰዎች ልከው፣ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና” ሲሉ ለመኑት።

39 ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜም ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍል አወጡት። መበለቶቹም ሁሉ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር በነበረችበት ጊዜ ያደረገቻቸውን ቀሚሶችና ልብሶች እያሳዩት ዙሪያውን ከበው ያለቅሱ ነበር።

40 ጴጥሮስም ሁሉንም ከክፍሉ አስወጥቶ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ፣ “ጣቢታ፤ ተነሺ” አለ። እርሷም ዐይኗን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች፤

41 እርሱም እጇን ይዞ አስነሣት፤ አማኞችንና መበለቶቹንም ጠርቶ ከነሕይወቷ አስረከባቸው።

42 ይህም ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ።