1 ፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር።
2 ሆኖም፣ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር።
3 እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፣ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው።
4 በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል?
5 ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትየዋንም ነቀፏት።
6 ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፣ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች።