19 ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም።
20 ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር።
21 በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ።
22 የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት።
23 ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት።
24 እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት።እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት።
25 ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው።