30 “ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ሁሉ ይበትናል።
31 ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም።
32 ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም።
33 “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ።
34 እናንት የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና።
35 መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር በጎ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገር ያወጣል።
36 ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል።