28 “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው። “አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።
29 “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤
30 ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”
31 ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ቦታ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች።
32 የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም፣ ስታድግ ግን ከቊጥቋጦዎች ሁሉ በልጣ፣ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ እስኪያርፉ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።”
33 አሁንም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።”
34 ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምሳሌም ሳይጠቀም የነገራቸው አንድም ነገር አልነበረም።