ማቴዎስ 19:3-9 NASV

3 ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “ለመሆኑ አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን መፍታት ተፈቅዶአልን?” ሲሉ ጠየቁት።

4 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?

5 እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን?

6 ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”

7 እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍቺውን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት።

8 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤

9 እላችኋለሁ፤ በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፣ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”