14 በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፤
15 “የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣
16 በጨለማ የሚኖር ሕዝብ፣ታላቅ ብርሃን አየ፤በሞት ጥላ ምድር ላለው፣ብርሃን ወጣለት።”
17 ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ኢየሱስ፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” እያለ መስበክ ጀመረ።
18 ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር።
19 ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።
20 ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት።